በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተሰጠ
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በ2019 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት (Life Skills) ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናው በትምህርት ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ልማት ክፍል በትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የሥልጠናው አስተባባሪና የሥራ ፈጠራ ልማት ክፍል ኃላፊ መምህር ሾዋንግዛው ጌታቸው እንደገለጹት፣ ሥልጠናው በሕይወት ክህሎት፣ በንባብና የጥናት ዘዴዎች፣ በጊዜ አጠቃቀም እና በጥሩ የግንኙነት ክህሎት ላይ ያተኮረ ነው።
በሥልጠናው የተሳተፉት ተማሪዎች ገመቹ ቶላሳ እና ላይሊሳ ገርባ በበኩላቸው፣ ሥልጠናው ጊዜያቸውን በአግባቡ ለማቀድ፣ ውጤታማ የጥናት ዘዴዎችን ለመከተልና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር ተጨማሪ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል።
ሥልጠናው አዲስ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው የግቢ ሕይወት ጋር እንዲላመዱና ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲከታተሉ ለማገዝ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።